ሐሰት፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ያጋሩ ይሸለሙ” በሚል የ50 ሺ ብር ሽልማት አላዘጋጀም
የ2014 አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቴሌግራም ቻናሉን ለሚቀላቀሉ ሰዎች “ያጋሩ ይሸለሙ” በሚል መርሃ ግብር የ 50ሺ ብር የገንዘብ ስጦታ ማዘጋጀቱን ከ 40ሺ በላይ ተከታዮች ያሉት “የኢትዮጵያ አየር መንገድ Ethiopian Airlines” የሚል ስያሜ ያለው የቴሌግራም ቻናል ጽፏል።
በተመሳሳይ ስያሜ ግንቦት 5፣ 2012 አ/ም የተከፈተው የቴሌግራም ቻናል በዚሁ ማስታወቂያው “እስከ መሰከረም 30 2014 የሚቆይ 1 ሺ ሰዎችን እድለኛ የሚያደርግ ፕሮግራም” መዘጋጀቱንም ያትታል።
ሆኖም በቴሌግራም ቻናሉ ላይ ብቻ ከ 311ሺ በላይ ሰዎች የተመለከቱት ማስታወቂያ ሐሰት መሆኑ ተረጋግጧል።
አየር መንገዱ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ በኩል የቻናሉንና ማስታወቂያውን ሐሰተኝነት የሚያረጋግጥ ጽሁፍ ያጋራ ሲሆን ትክክለኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቴሌግራም ቻናል ከ 23ሺ400 በላይ ተከታዮች አለው። የተከፈተውም በመጋቢት 21፣ 2011 አ/ም ነው።
በምስሉ ላይ እንደሚታየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻናሉ በሐሰት የተከፈተ እንደሆነ ድርጊቱም የማጭበርበር ተግባር መሆኑን በይፋ አረጋግጧል።
This fact-check was produced by Addis Media in partnership with Code for Africa.